የኸሚስ ወጎች

የኸሚስ ወጎች

Sep 4, 2025

ረኡፍ ፡ ረሒም

ለእርሳቸው ብቻ ከተገቡ ስሞች መሃከል የሚመደቡ ሩኅሩኅ እና አዛኝ የሚል ፍቺ ያላቸው ስማቸው ሲሆን ከዚሁ ተያያዥ የሆኑ ነብዩ-ራሕማ፣ ረሱሉ-ራሕማ፣ ረሱሉል መርሐማ፣ ራሕመተል ኡምማ፣ ራሕመተል ዓለሚን የሚጠሩበት ስም ነው። ደረጃቸው ከፍፍ ማለቱ፣ ልእቅና እና ግርማቸው መናኘቱ ነው ስማቸውን ያበዛው። የስም መብዛት የግብር መስፋት ሆኖ ነው እስከ 99 ወይም 202 ድረስ ሰዎች የሰዪዳችንን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስሞች ቆጥረው የደረሱት።

"ለዓለማት እዝነት አድርገን እንጂ አልላክንህም" አንቢያ 107

አላህ ለፍጥረታት ሲያዝን ሐቢቡላህን ወደ'ሱ ይጠሯቸው ዘንድ ላከ። በእሳቸው መምጣት እምነተቢስ ሆኖ መንፈሱ ሞቶ የነበረው ማሕበረሰብ አንሰራራ። የመፈጠሩ ዓላማ ጠፍቶት መንገድ ስቶ ሲተራመስ የነበረ ኸልቅ ሁላ በእሳቸው ሰከነ። የእዝነት ነብይ ናቸው፡ እንኳን ላመኑባቸው ቀርቶ ለሚዋጓቸው ከሀዲያን ሳይቀር የሚራሩ። ለዓለማት እዝነት ናቸው፡ እንስሳት ብሶታቸውን የሚዘረግፉላቸው፡ እሳቸውም ሐቃቸውን የሚያስመልሱ፡ ሕፃናት ይወዷቸዋል፡ እሳቸው ያፈቅሯቸዋል፡ እርግብ የሞተበትን ብላቴና ጎንበስ ብለው እያፅናኑ የሚዳብሱ። ለፍጥረታት ሁሉ ማዘንን ያስተማሩ ሩኅሩኅ ነብይ..

لَقَدْ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مِّنْ أَنفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُم بِالْمُؤْمِنِينَ رَءُوفٌ رَّحِيمٌ

"ከጎሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን (ላይ) ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ"

የእሳቸው ኡመት ምን ኃጢአት ቢያበዛ ምድር ላይ ጥፋት አይላክበትም። ከሃዲም ሆነ መናፍቅ ከእሳቸው እዝነት መጠለሉ አይቀርም።
"አላህም አንተ በውስጣቸው እያለህ የሚቀጣቸው አይደለም..."

አላህ የአማኞችን ልብ በኢማን ያሸበረቀው፣ አላህን በማወቅ ሀሴታቸውን ያደመቀው፣ እሳቸውን አስወድዶ የመረጠውን ያነገሰው፣ ምንዳቸውን ያለ ሒሳብ የለገሰው፣ ተቆጥሮ የማያልቅ ጸጋ ያፈሰሰው በአሽረፈል ኸልቅ ምክንያት ነው።
"እኔ የእዝነት ነብይ ነኝ" የሚሉት ሐቢቡላህ ሁሌም ወደ እዝነት ይጣራሉ። አማኞች በቻሉት መጠን ለፍጥረታት እንዲያዝኑ ያስተምራሉ።
"አዛኞችን አዛኙ ጌታ ያዝንላቸዋል"
"አላህ ከባሮቹ መሀከል አዛኞችን ይወዳል"
"የማያዝን አይታዘንለትም" ከእዝነት አስተምህሮዎቻቸው በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።


اللهم صل على سيدنا محمد عدد ما فى علم الله


ኢፋዳ ኮምዩኒኬሽን